ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት አንደበት – ካለፈው የቀጠለ

“ሕማምን፣ ሞትን ገንዘብ አደረገ፤ በሥጋው የሞተው ሞትም የእኛን ባሕርይ በመዋሐዱ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፤ ሞት ሰው የመኾን ሥራ ነውና፡፡ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመኾን ሥራ ነውና፤ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን /ሞትንና ትንሣኤን/ እናውቃለን፤” (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፴፭)፡፡ “በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደ ኾነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፡፡ ይህ ለመለኮት አይነገርም፤ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፤” (ዝኒ ከማሁ ፸፱፥፱)፡፡ “የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን (ኃጢአትን) ሻረ፡፡ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ (ፍዳ መርገምን አጠፋ)፡፡ ሲኦልን በዘበዘ፡፡ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፡፡ የምሕረትን በር ከፈተ፤ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዂሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚኾን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፤” (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፫፥፮)፡፡ “ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ እንደ ተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደ ኾነ፤ መድኀኒታችን በሚኾን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደ ሰጠን እናምናለን፡፡ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ዂሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ዂሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከኾነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ት ንሣኤም ሐሰት ከኾነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፡፡ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደ መኾኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደ መኾኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከ...